1ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ ዜፋውያን መጥተው ለሳኦል። እነሆ ዳዊት በእኛ ዘንድ ተሸሽጓል ብለው በነገሩት ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት።
አቤቱ፥ በስምህ አድነኝ፥ በኃይልህም ፍረድልኝ።
2አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማኝ፥ የአፌንም ቃል አድምጥ፤
3እንግዶች ቁመውብኛልና፥ ኃያላንም ነፍሴን ሽተዋታልና። እግዚአብሔርን በፊታቸው አላደረጉትም።
4እነሆ፥ እግዚአብሔር ይረዳኛል፥ ጌታዬም ለነፍሴ ደጋፊዋ ነው።
5ክፋትን ወደ ጠላቶቼ ይመልሳታል፤ በእውነትህም አጥፋቸው።
6ከፈቃዴ እሠዋልሃለሁ፤ አቤቱ፥ መልካም ነውና ስምህን አመሰግናለሁ፤
7ከመከራ ሁሉ አድኖኛልና፥ ዓይኔም በጠላቶቼ ላይ አይታለችና።